
ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በይርጋዓለም ከተማ የተገነባውን የጽሩይ ሳሙናና ዲተርጀንት ፋብሪካ መርቀው ከፈቱ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሲዳማ ሀገረ ስብከት በይርጋዓለም ደ/ታቦር ኢየሱስ ወደብረ መንክራት ቅድስት አርሴማ አብያተ ክርስቲያናት ሰበካ ጉባኤ የተገነባው ጽሩይ የሳሙናና ዲተርጄንት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት የሀይማኖት ተቋማት በእንደነዚህ አይነት ስራዎች መሳተፋቸው በልማት ራስን የመቻልና ከልመና የመውጣትን ተሞክሮ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው እንደገለፁት ፋብሪካው ቤተ ክርስቲያን ድህነትን ለመቀነስ በኢንዱስትሪ ልማት የሚኖራት አስተዋጽኦ ጉልህ ለመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል።
ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተደረገበት ዘመናዊ ፋብሪካው ቤተ ክርስቲያን በምጣኔ ሀብት ራሷን የምትችልበትን በር የሚከፍት እንደሆነም ተገልጿል ።
ፋብሪካው የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ከማገዝ ባሻገር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ እድል እንደሚፈጥርም የፕሮጀክቱ ሃላፊ ዶ/ር ታደሰ ፋንታዬ ጠቅሰዋል።
ህዳር 07-2017 ዓ.ም
ሀዋሳ