የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ዳራ፤
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተመሰረተው በ2008 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ጽ/ቤት በሚል ስያሜ ሲሆን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በክልሉ ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የክልሉን ህዝብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ድርሻውን ሲወጣ ቆይቷል፡፡ ሲዳማ በክልል መደራጀቱን ተከትሎ የኮሚሽኑን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው ደንብ ቁጥር 8/2013 የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በሚል ስያሜ ተደራጅቶ ወደ ስራ በመግባት በክልሉ መንግስት የተሰጠውን የክልሉን ኢኮኖሚ ማሳደግ፣ ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የማድረግ ተልኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
ውስጣዊ አደረጃጀቱንም በተመለከተ ኮሚሽኑ በሶስት ዋና ዳይሬክቶሬቶች ማለትም የኢንቨስትመንት መሬትና ፖቴንሺያል ጥናት ዳይሬክቶሬት፣የኢንቨስትመንት ፍቃድ መረጃና ፕሮሞሽን ዳይሬክቶሬት፣የኢንቨስትመንት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬትና በአምስት ድጋፍ ሰጪ ዳይሬክቶሬቶች የተዋቀረ ሲሆን የበላይ አመራሮችን ጨምሮ 40 ወንዶችና 25 ሴቶች በድምሩ 65 ሰራተኞች አሉት፡፡
ኮሚሽኑ ለኢንቨስትመንት አገልግሎት የሚውል የገጠርና የከተማ መሬት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ያሰባስባል፣ወደ መሬት ባንክ ያስገባል፤በህግ አግባብ ለኢንቨስተሮች ያስተላልፋል፣ የክልሉን ሀብት በጥናት በመለየት መረጃ ይይዛል፤ መረጃውን ለሚፈልግ አካል ያስተላልፋል፣የክልሉን የኢንቨስትመንት አማራጭ እድሎችን ያስተዋውቃል፣ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ይሰጣል፣ ይለውጣል፣ይተካል፣ይሰርዛል እንዲሁም ፍቃድ ወስደው ወደ ስራ ለገቡ ፕሮጅክቶች ድጋፍና ክትትል ያደርጋል፣ የማበረታቻ ድጋፍ የመስጠት ስራ እና ሌሎችንም ይሰራል፡፡